ስለ ባለስልጣን መ/ቤቱ

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የግብርና ጥራትና ደህንነት ባለስልጣን በአዋጅ በ208/2006 እና በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 264/2011 የተቋቋመ ሲሆን ከ2007 ዓ/ም መግቢያ ጀምሮ ወደ ስራ ገብቷል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥራትና ደህንነቱ የተረጋገጠ የግብርና ግብዓት ያለውን የጎላ ድርሻው ታሳቢ በማድረግ በግብርና ግብዓት ላይ የጥራት ማረጋገጥ ስራ እንዲያከናውን፣ የኳራንቲን ተባዮች ክስተት አስከፊ በሆነ መልኩ እየሰፋ በመምጣቱ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የግብርና ግብዓቶችን የተመለከቱ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም መስፈርቶች በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ በማስፈለጉ፣ የህግ ማዕቀፉን ከሚያስፈፅሙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለሥራው ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ለማድረግ እና ነፃ ፣ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን የሚወስድ አካል መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ተቋቁሟል፡፡ ተቋሙ በባለስልጣን መ/ቤትነት ደረጃ ከመቋቋሙ በፊት በተለያዩ ስያሜዎች፣ ደረጃዎችና ተጠሪነቶች ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቀይቷል፡፡ በብሄራዊ የግብርና ግብዓት ባለስልጣን ስር ተመሳሳይ ስያሜ በመያዝ በክልሉ አራት ከተሞች (ደሴ፣ ጎንደር፣ ደ/ማርቆስና ዱርቤቴ ከተሞች) ባላራቶሪዎችን በመክፈት ከ1995 እስከ 1996 ዓ/ም ለሁለት ዓመት አገልግሎት የሰጠ ሲሆን ከ1996 እስከ 2000 ዓ/ም ድረስ በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ስር የግብርና ግብዓት ግብይት መምሪያ በሚል ስያሜ ለአራት አመታት አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በመቀጠልም እንደ ሀገርየበBPR አደረጃጀት መተግበርን ተከትሎ የጥራት ቁጥጥር ሥራውን የእንስሳትና ዕፅዋት ኳራንቲን ኢንስፔክሽን ጤናና ጥራት ቁጥጥር በሚል ስያሜ በሥራ ሂደት ደረጃ ተደራጅቶ ከ2001 ዓ/ም እስከ 2004 ዓ/ም ለ3 ዓመታት አገልግሎት የሰጠ ሲሆን ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ ባለስልጣን ሆኖ እስከተቋቋመበት 2006 ዓ/ም ድረስ መጠነኛ የስያሜ ለውጥ በማድረግ የዕፅዋት ኳራንቲን ኢንስፔክሽን ጤናና ጥራት ቁጥጥር የሥራ ሂደት በመባል በግብርና ቢሮ ስር የግብርና ግብዓቶችን ጥራት የማስጠበቅና የፋይቶ ሳኒተሪ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡

Scroll to Top