የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የክልል ቴክኒክ ቡድን በወቅታዊ የግብርና ስራዎች ላይ ያደረገው የመስክ ድጋፍ ግብረ መልስ የቢሮው አመራሮች፣ ዳይሬክቶሬቶችና ባለሙያዎች በተገኙበት ተገምግሟል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እንደገለፁት ወቅቱ የሚጠይቀውን ተልዕኮ የሚሸከምና የሚፈፅም ተቋም መገንባት ይኖርብናል ብለዋል። በዚሁ ትይዩ በየደረጃው ያለ ባለሙያም አቅዶ የሚሰራና ውጤት የሚያመጣ መሆን ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል። የተቋም ግንባታ አካል የሆኑት የግብርና ኤክስቴንሽን አደረጃጀቶች ዋነኛ የተግባር ማስፈፀሚያ አቅሞቻችን በመሆናቸው ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰዋል።
ከመስኖ ልማት አኳያ ፀጋዎቻችንን እንለይ ያሉት አቶ ደረጀ ማንደፍሮ አዲስ መስኖ እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የርብርብ ማዕከል መሆን ይገባል ነው ያሉት። የመስኖ ማልሚያ ዘዴዎችን በመለየት በጊዜ የለንም ስሜት መስራት በጣም ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተዋል። የመስኖ ውሃ አጠጣጥ ዘዴዎችን ማዘመን ያስፈልጋል ብለዋል።
የግብርና ሜካናይዜሽን ሌላኛው የርብርብ ማዕከል ሲሆን አርሶ አደሩ ከአነስተኛ ቴክኖሎጂ ጀምሮ እንዲጠቀም ማድረግ አለብን ብለዋል። ፍላጎት መፍጠርና አርሶ አደሩ እንዲቆጥብ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ ቢሮ ሀላፊው በአፅንኦት ተናግረዋል።
የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት በተለይም ደግሞ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ በንቅናቄ ማስጀመር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት ምጣኔ ከፍ እንዲል ክትትልና ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ሌሎች ተግባራትም ቤቴን በራሴ አቅም የFTC ግንባታ፣ የምግብና ስርዓተ ምግብ፣ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት እና የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት መፈፀም እንዳለባቸው አቶ ደረጀ ማንደፍሮ አሳስበዋል።
በግምገማ መድረኩ የየዞኖች የመስክ ድጋፍ ሪፖርት ቀርቧል። የበጀት ዓመቱ 3ኛ ዙር የመስክ ድጋፉ ለየት የሚያደርገው ተደግፈው የማያውቁ ዞኖችና ማዕከላት የድጋፉ አካል መሆናቸው ተገልጿል።
በ3ኛው ዙር የክልል የባለሙያዎች ቴክኒክ ቡድን 17 ዞኖች፣ 22 ወረዳዎችና 44 ቀበሌዎች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
መረጃው የግብርና ቢሮ ፌስ ቡክ ገፅ ነው

