የአርሶ አደሩን የዘር ፍላጎት ለመሸፈን የመነሻ ዘር ብዜት ተግባርን ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጅ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይሬክቶሬት ዓመታዊ የመነሻ ዘር ብዜት ስራ አፈጻፀምን አጋር እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ግምገማ አካሄደ

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አስማረ ደጀን የክልላችን የኢኮኖሚ መሰረት የግብርናዉ ዘርፍ መሆኑን በመግለፅ ተፈላጊዉን ዉጤት ለማምጣትም የዘር ብዜት ስራችን ላይ በማተኮር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለዩ የሰብል ዓይነቶችን የመነሻ ዘር ብዜት በጥራትና በስፋት ማከናወን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክቶሩ አክለዉም ኢንስቲትዩቱ በ29 ሰብሎች ላይ 174 ዝርያዎችን ቢያስለቅቅም የዘር ብዜት ስራችን የክልላችንን አርሶ አደር የዘር ፍላጎት መሰረት ያደረገ እና ጥራቱን የጠበቀ ዘር ከማቅረብ አኳያ ዉስንነቶች እንዳሉ ጠቁመዉ ለቀጣይ ተግባራችን በብዜት ስራ ላይ የተሰማራን አካላት ክፍተቶቻችንን በዚህ ዉይይት በመለየት ተጠናክሮ ወደ ስራ መግባት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጅ ብዜትና ዘር ምርምር ዳይርከቶሬት ዶ/ር ሰማኝ አስረዴ በበኩላቸዉ የኢንስቲትዩቱን ዓመታዊ የመነሻ ዘር ብዜት ስራ አፈፃፃም በሰብል ዓይነትና የመሬት ሽፋን ሪፖርት ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ከዉይይቱ የተገኘዉ ግብዓትም ካለዉ ክልላዊ የፀጥታ ሁኔታ አኳያ በሪፖርቱ የቀረቡት ስራዎች እና የተገኙ ዉጤቶች አበረታች እንደሆነ ታይቷል፡፡ ዶ/ር ሰማኝ አስረዴ በበኩላቸው የተሳታፊዎችን አስተያየት በመቀበል ለተመዘገበዉ ዉጤት በዘርፉ የተሰማራን አጋርና ባለደረርሻ አካላት ተቀራርበን በመስራታችንና የጋራ እቅድ በማዉጣታችን የተገኘ ዉጤት ነዉ ብሏል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለዉም የክልሉን የዘር ፍላጎት ለማሟላት በኢንስቲትዩቱ በቅርቡ የተለቀቁ የሰብል እና የመኖ ዝርያዎችን በመለየት የመነሻ ዘር ብዜት እና አቅርቦት ትኩረት አድረገን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በዉይይት መድረኩም የክልሉ ግብርና ቢሮ፤ የመንግስት ዘር አባዥ ተቋማት፤ ዘር አባዥ ዩኒዮኖች፤ የዘር ጥራትና ደህንነት ባለስልጣን እና በኢንስቲትዩቱ ስር ያሉ ሁሉም የግብርና ምርምር ማዕከላት በበጀት ዓመቱ የሰብል የመነሻ ዘር ብዜት አፈፃፀም ሪፖርት በማቅረብ ዉይይት ተካሂዷል፡፡ እንደዚሁም የግብርና ጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን ባ/ዳር ቅርንጫፍ በበኩሉ በኢንስቲትዩቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የመነሻ ዘር ብዜት ስራዎች በተቀመጠዉ ስታንዳርድ መሰረት መከናወናቸዉን ያደረገዉን የክትትል እና ቁጥጥር ስራ ሪፖርት ለውይይት የቀረበ ሲሆን ግኝቱም አበረታች እንደነበር ተገልጿል ፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይ የሚከሰቱ ክፍተቶችን በማረም ጥራቱን የጠበቀ የዘር ብዜት ስራ እንዲከናወን ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመቀራረብ እና በመቀናጀት እንሚሰራ ገልፆል፡፡

በመጨረሻም ከኢንስቲትዩቱ ጋር የመነሻ ዘር ብዜት ስራን በቅንጅት የሚያከናዉኑ ተቋማትና ማህበራት ለቀጣይ የበጀት ዓመት የመነሻ ዘር ብዜት እቅድ በማቅረብና በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡

ምንጭ፡- ከግብርና ምርምር እንስቲቱት ድህረ-ገፅ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top